ጤንነት
አንድ ሰው ጤናው እንደተጓደለ ወይንም እንደታመመ ከሚያረጋግጥባቸው ዋና ዋና ምልክቶች ውስጥ አንዱ የምግብ ፍላጎት ማጣቱ ነው። የተፈጠርነው እንድንበላ ተደርገን ነው። ይሄ ሰውነታችን የተሰራው፥ በየቀኑ እየበላ እንዲበረታ ተደርጎ ነው። ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእኛ የሚሰራው አምላክ ደግሞ፥ ተገደን ሳይሆን ወደንና ፈልገን እንበላ ዘንድ ምግብ የመብላት ፍላጎትን ወይንም ረሀብን በውስጣችን አስቀምጧል። መራብ በረከት ነው፥ መብላት መፈለግ ጤንነት ነው። ምክኒያቱም ምንም ቤታችን በብዙ ምግብ ቢሞላም እንኳን፥ የመብላት ፍላጎታችን ከተዘጋ ልንበላ አንችልም።
አሁን ባለሁበትና ከእግዚአብሔር ጋር ጉዞ በጀመርኩበት በዚህ ሕይወት ውስጥ ምንም ፍላጎቴ ሁልጊዜ መንፈሳዊ መነቃቃትና ግለት ውስጥ መሆን ቢሆንም፥ አንዳንዴ ግን በራሴ ምድራዊ ሕይወት ጉዳዮች ዙሪያ የምወጠርባቸውና አይምሮዬ በሌሎች የተለያዩ ነገሮች የሚያዙባቸው ወቅቶች አሉ። ታዲያ ግን ትልቅ ፍርሀት ውስጥ የምገባው፥ ከእግዚአብሔር ጋር ለመራመድ የተሰጠኝ እድል የሚገባኝ መስሎ ሲሰማኝ፣ አምላክ ስለ ራሴ በደልና ኃጢያት ሰው በመሆኑ ሚስጥር መደነቅ ሳቆም፣ ድሮ እያለቀስኩ የምዘምራቸው መዝሙሮች ትርጉም ሲጠፋብኝ፣ በእግዚአብሔር መገረም ሳቆም፣ የተደረገልኝን ሁሉ ከእግዚአብሔር እጅ መቀበሌ የሚገባኝ መስሎ ሲሰማኝ፣ በቃ ዝም ብዬ ስወጣና ስገባ፣ ውስጤ እግዚአብሔርን የመፈለግ ስሜትና ረሀብ ሲያጣ፥ የዚያን ጊዜ እንደታመምኩ ይገባኝና እፈራለሁ። አይ ለካ አልታወቀኝም እንጂ ነፍሴ ህመም ውስጥ ናት እላለሁ። ይሄ ጤንነት አይደለም። ጤንነትማ የእኔ እጅ የሌለበትን ስጦታ ከእግዚአብሔር እጅ በመቀበሌ ሁልጊዜ ልቤ ውስጥ ያለው መደነቅ ነው። በማይገባኝ ስፍራ ላይ በመቀመጤ ውስጥ ያለው የልብ ምስጋና ነው። የመንፈሳዊ ጉዞዬ ጤንነት ዋናው መለኪያው ደግሞ እግዚአብሔርን መፈለጌ ነው። ውስጤ ያለው መንፈሳዊ ረሀብ ነው።
ሰው ታዲያ ታሞ ምግብ የመብላት ፍላጎት ሲያጣ፥ ያ ጤንነቱና የመብላት ፍላጎቱ በትክክል ወደ እርሱ እስከሚመለስ ድረስ ቢያንስ ቀለል ያሉ ምግቦችን በትንሽ በትንሹ ቀስ ቀስ እያለ በመብላት እራሱን ያድናል እንጂ፥ ወደ ሞት እስከሚወርድ ድረስ እጁን አጣምሮ ቁጭ ብሎ አያይም። ስለዚህ ሌሎች ነገሮቼን ቀነስ አድርጌ እንደገና እግዚአብሔርን መሻቴ ፥ እግዚአብሔርን መፈለጌ እስኪመለስልኝ፥ የመንፈሳዊው አለም ሚስጥር እንደገና በልቤ እስከሚከብድ፣ እንደገና የመስቀሉ ፍቅር ሀይል በልቤ እስኪበረታ ድረስ ዝም ብዬ በአምላኬ ፊት ልቤን አረጋለሁ። ዝማሬዎችን እሰማለሁ፣ ወደ ጸጥታ ቦታዬ እገባና ዝም ብዬ እቀመጣለሁ፣ ቢገባኝም ባይገባኝም ቃሉን ዝም ብዬ አነበዋለሁ፣ በእግዚአብሔር ፊት እውነተኛ በመሆን ስላመመኝ እንዲፈውሰኝ እጠይቀዋለሁ።
የእግዚአብሔር ቃል ግልጽ አድርጎ በአንደኛ ቆሮንቶስ ምእራፍ አንድ ላይ እንደሚናገረው፥ ለፍጥረታዊው ሰው የእግዚአብሔርን መንፈስ ነገር ሞኝነት ነው። ሊቀበለውም ሊያውቀውም ሊደነቅበትም አይችልም። በዚህ አለም ሲስተም ለተያዘና በጣም ጥበበኛ የሆነ ለመሰለው እንዲሁም ወደ ጥፋት ጎዳና እየሄደ እንዳለ ላልገባው ሰው እኮ የመስቀሉ ቃል እራሱ ሞኝነት ነው። አለም በጥበብዋ አምላክን ስላላወቀች የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ማዳን ሆነ። ለካ መንፈሳዊ ነገር በሞኝነት እግዚአብሔርን እና ስራውን ማመን ብቻ ነው። እንዲያውም እዚያው የ1ኛ ቆሮንቶስ መጽሐፍ ላይ ሲናገር፥ “ማንም ራሱን አያታልል፥ ከእናንተ ማንም በዚች አለም ጥበበኛ የሆነ ቢመስለው፥ ጥበበኛ ይሆን ዘንድ ሞኝ ይሁን” ይላል። ጥበብ ጥበበኛ መሆን አይደለም፥ እውነተኛው ጥበብ የራሳችንን ጥበብ ጥለን በሞኝነት በእግዚአብሔር ፊት የምንመላለስበት የዋህ የሆነው ልባችን ነው። እውነተኛው ጥበብ፣ እራስን በእግዚአብሔር ፊት ባዶ በማድረግ ማቅረብ ነው። የጥበብ እራሱ መጀመሪያው እግዚአብሔርን መፍራት ነው። እውነተኛ የሆነው መንፈሳዊ ጥበብ ሲጀምር፥ የሚጀምረው እራሱ እግዚአብሔርን ከመፍራት ነው።
እዚሁ የአንደኛ ቆሮንቶስ መጽሐፍ ላይ ስለ አለም ጥበብና ስለ እግዚአብሔር ጥበብ ሲናገር፥ መንፈሳዊ እና ዓለማዊ ጥበብ፥ ሁለቱም ስማቸው ጥበብ ተብሎ ይጠራ እንጂ ፍጹም ተቃራኒ እና የሚቀዋወሙ ነገሮች ናቸው። አንድ ሰው መንፈሳዊ በሆነው ጥበብ ሲሞላ፥ የአለም ነገር በሙሉ ሞኝነት እንደሆነ ይረዳል። ምክኒያቱም የዚህች አለም ጥበብ በእግዚአብሔር ፊት ሞኝነት ነው በማለት እዚሁ አንደኛ ቆሮንቶስ ምእራፍ 3 ላይ ይናገራል። አንድ ሰው ደግሞ በዚህች አለም ጥበብ ሲሞላ፥ መንፈሳዊው ነገር ጨዋታና ሞኝነት መስሎ ሊታየው ይጀምራል። እምነት የሚባለው ክቡር ነገር በፊቱ ሞኝነት ሆኖ ይቆጠራል። የዘላለሙንና ትልቁን የእግዚአብሔር ሀሳብ በጊዜያዊው ነገር ብልጫ ሊያየው ይገደዳል። በእነዚህ ምልክቶች መሰረት፥ ውስጣችን እያመዘነ ያለው ወደ መንፈሳዊው ጥበብ ነው ወይንስ ወደ ስጋዊው ጥበብ የሚለውን መመዘን እንችላለን ማለት ነው።
የምግብ ፍላጎታችን ምግብ እንድንበላ ይረዳናል፥ መብላታችን ደግሞ በሕይወት ያቆየናል። እግዚአብሔርን መፈለጋችን ከእግዚአብሔር ጋር እንድንሆን ያደርገናል፥ ከእግዚአብሔር ጋር መሆናችን ደግሞ በሕይወት ያኖረናል። መጽሐፍ ቅዱስ በመዝሙረ ዳዊት ምእራፍ 105፡4 ላይ ሲናገር “እግዚአብሔርን ፈልጉ ትጸናላችሁም፤ ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ” በማለት እስከመጨረሻው መጽናት ያለው እርሱን በመፈለግ ውስጥ መሆኑን ግልጽ አድርጎ ይናገራል።
እግዚአብሔርን መፈለግ ማለት ታዲያ ምን ማለት ነው? ብለን ከጠየቅን፥ እግዚአብሔርን መፈለግ ማለት፥ የመጸለይ ወይንም ቃል የማንበብ ፍላጎት እስኪሰማን ቁጭ ብሎ መጠበቅ ማለት አይደለም። ውስጣችን ያለው እግዚአብሔርን የመፈለግ ረሀብ መፈለጋችንን ቀላል ቢያደርግልንም፥ ረሀቡ ውስጣችን ከሌለ ግን እስኪርበን መጠበቅ የለብንም። ፍላጎትን ወይንም ረሀብን እግዚአብሔር እንዲሰጠን እየጸለይን ፊቱን የመፈለግ ድርጊታችንን እንቀጥላለን። እግዚአብሔርን መፈለግ ሲሰማን ብቻ የምናደርገው ነገር አይደለም። እንደዚያ ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር ፊቴን ፈልጉ ብሎ በትእዛዝ መልክ አይሰጠንም ነበር። እግዚአብሔርን መፈለግ በእኛ ውሳኔ እና ድርጊት ውስጥ የሚገለጥ እንድናደርገው የታዘዝነው የእግዚአብሔር ትእዛዝ ነው። መፈለግ ማለት፥ ያ የምንፈልገውን ነገር እስከምናገኝ ድረስ የምናደርገው ያላሰለሰ ጥረት ማለት ነው። “ቆይቼ የእግዚአብሔርን ደጅ ጠናሁት” ብሎ መዝሙረኛው በመዝሙሩ እንደተናገረ፥ እግዚአብሔር ደጅ ላይ መቆየት፣ እግዚአብሔር እንደሚሰማን አምነን ከእግዚአብሔር ጋር ማውራት፣ ሌሎች ነገሮችን እየቀነስን መንፈሳዊ ትምህርቶችን እንዲሁም ዝማሬዎችን መስማት፣ እግዚአብሔር ወደሚገኝባቸው መንፈሳዊ ሕብረቶች መሄድ፣ እግዚአብሔርን ወደምናገኝባቸው ሰዎች መጠጋት፣ ድካም ሲሰማን እና መጸለይ ሲያቅተን ከሰዎች ጋር መጸለይ፥ እነዚህ ሞኝነት የመሰሉ ነገር ግን ሕይወት የሚገኝባቸው መንፈሳዊ ጥበቦች ናቸው። ከእግዚአብሔር ጋር ለመዝለቅ ይረዳን ዘንድ እግዚአብሔርን ለመፈለግ የምንሄድባቸው ርቀቶች ናቸው።
እንዲያው እኛ ማድረግ ያለብንን የራሳችንን ሀላፊነት ተነጋገርን እንጂ እኮ፥ ፈልጉኝ ታገኙኛላችሁ ያለው አምላክ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ስናደርግ በእውነተኛ ልብ ለፈለጉት እኮ ያን ያህል ደጅ የሚያስጠና አምላክ አይደለም። በእውነተኛ ልብ የፈለጉት ሰዎች በሙሉ እንዳገኙት መስክረውልናል። በትጋት የፈለጉት ሰዎች በሙሉ ነፍሳቸው በቅቤና በስብ እንደሚረካ መርካታቸውን ተናግረዋል። በመገኘቱ ውስጥ ያለውን እርካታ ደግሞ የእኛም ነፍስ ሕያው ምስክር ናት። ለካ የሚያስፈልገኝ ሌላ ነገር አልነበረም። ይሄ ነው በቃ ለእኔ የሚያስፈልገኝ። የእኔ ትክክለኛ ቦታ ይሄ ነው። እዚህ ጋር ለመሆን ነው የተፈጠርኩት። ይሄንን እግዚአብሔርን በማግኘት ውስጥ ያለውን እርካታ በገንዘብ፣ በእውቀት፣ በትዳር፣ በቁሳቁስ አላገኘውም የሚያስብል እና ሌላ ነገር ሊሞላ የማይችለውን የነፍሳችንን ክፍተት የሚሞላ ብቸኛው ነገር የእግዚአብሔር መገኘት ነው። እርሱን ለመፈለግ የሄድንባትን ትንሽ ርቀት፥ በብዙ የመገኘቱ ጠል ሲያረሰርሰን፥ ይሄ ፍላጎት የምንለው ነገር የየእለት ተግባራችን መሆን ይጀምራል።
ይሄ አሁን የምመሰክርላችሁ፥ የማላጋንነው ሳልጨምርና ሳልቀንስ የምናገረው የእኔ የግል ሕይወቴ ምስክርነት ነው። ብዙ የጸሎት ርእሶች አሉኝ። ብዙ እግዚአብሔር እንዲያደርግልኝ የምፈልጋቸው ጥያቄዎች በህይወቴ ውስጥ አሉ። አንዳንድ ጊዜ ግን እነዚያን ማለቂያና ማብቂያ የሌላቸውን ጥያቄዎቼን ወደጎን አስቀምጪ፥ እግዚአብሔርን ለመፈለግ ብቻ ወደ ጸሎት ቦታዬ እሄዳለሁ። እንደዚህ በማደርግባቸው ቀናቶች፥ ሌላ ነገር ሳደርግ የማላገኘው ይሄንን በማድረጌ ብቻ የማገኘው ልዩ የሆነ የእግዚአብሔር መገኘት አለ። የዚያን ቀን በቃ የተለየ ነው። እፈልግሀለሁ ስለው ብቻ የሚገኝ ልዩ የሆነ በቃላት ማስቀመጥ የማልችለውን የእግዚአብሔርን ህልውና አውቀዋለሁ። ልክ ሰው የሚወደው ሰው ቤት ሄዶ መጎብኘት እና ከዚያ ከሚወደው ሰው ጋር ጊዜ ማሳለፍ እንደሚወድ ወዳጅ ሆኖ ባለሁበት ስፍራ በመገኘቱ ሙላት ይሆናል። የሚገኘው ሌሎች የጸሎት መልሶቼን ሊሰጠኝ አይደለም፥ የሚገኘው ራሱን ሊሰጠኝ ነው።
ስሜቱን ለመግለጽ ሞክሪ ከተባልኩ፥ ፍቅር እላለሁ። ዝም ባለው ህልውናው ውስጥ ፍቅር ጮክ ብሎ ይሰማኛል። ውስጤ ያለው ሰፊ የሆነ የመፈቀር ፍላጎት መልስ ሲያገኝ ይሰማኛል። እኔም በጣም ነው የምወድህ እላለሁ እየደጋገምኩ። አንዴ እስቃለሁ፣ አንዴ አለቅሳለሁ በቃ ውስጤ ሁኚ ያለኝን ሁሉ በፊቱ እሆናለሁ። ከዚያ ቦታ የትም መሄድ አልፈልግም። እዚያ ቦታ ዝም ብሎ መቀመጥ፥ ይሄን አርግልኝ፣ ይሄን ፈጽምልኝ ሳልል፣ በቃ እየተሰማኝ ያለውን መኖሩን በመንፈሴ እየሰማሁ ነፍሴን ከህልውናው ማርካት ብቻ ነው። ገና መንግስተ ሰማይ ሳልሄድ፥ እዚያ ስሄድ የሚጠብቀኝን ደስታ በጥቂቱ መለማመድ ነው።