Hi.

Welcome to my site! I hope and pray that the blogs I post encourages and uplifts you to keep building a deeper relationship with the Lord.

God bless you!

መስዋእት 

መስዋእት 

በሀገራችን አንድ የምወደው አባባል አለ። ሰነፍ ከራሱ ውድቀት ይማራል፥ ጠቢብ ግን ከሰው ውድቀት ይማራል ይላሉ። ምን ማለት ነው? አንዳንድ ጊዜ የሆነን ነገር ለመማር ግዴታ እኛ በዚያ ውድቀት ውስጥ ማለፍ ላይጠበቅብን ይችላል። ግዴታ ዋጋ መክፈል ላይጠበቅብን ይችላል። በዚያ ውድቀት ውስጥ ያለፉ ሰዎችን ሕይወት አስተውለን በመመልከት ብቻ ብዙ ነገሮችን መማር እንችላለን። ለምንድነው ነገራቸው የፈረሰው? ለምንድነው የወደቁት? ለምድነው ዋጋ የከፈሉት የሚለውን ምክኒያት በማስተዋል ብቻ እኛ ከብዙ ውድቀት እና ዋጋ መክፈል ልንድን እንችላለን። የምንማረው ከሰዎች ስኬት ብቻ አይደለም፥ አስተዋዮች ከሆንን ከሰዎች ውድቀትም ብዙ እንማራለን። መጽሐፍ ቅዱስ ይሄንኑ ሀሳብ በምሳሌ መጽሐፍ ምእራፍ 24፡30 ላይ ሲያስረግጥ እንዲህ ይላል፥ “በታካች ሰው እርሻ፥ አእምሮ በጐደለውም ሰው ወይን ቦታ አለፍሁ። እነሆም፥ ሁሉ እሾህ ሞልቶበታል፥ ፊቱንም ሳማ ሸፍኖታል፥ የድንጋዩም ቅጥር ፈርሶአል። ተመለከትሁና አሰብሁ፤ አየሁትና ተግሣጽን ተቀበልሁ።” አያችሁ፥ ይሄ ሰው ታካች በሆነ ሰው እርሻ ውስጥ ሲያልፍ፥ የተመለከተው ነገር ነበር። የዚያ ታካች ሰው እርሻ በእሾክ የተሞላ ነው፥ እርሻው በአረም ተሸፍኗል፣ የድንጋዩ ቅጥር ሁሉ ፈራርሷል። ለምንድነው ይሄ የሆነው? የእርሻው ባለቤት ታካች ነው፥ ሰነፍ ሰው ነው። ታዲያ ይሄ የዚህን ታካች ሰውዬ እርሻ ቆሞ የተመለከተው ሰው ምን አለ? የሰውዬውን የፈረሰ እርሻ በማየት ብቻ ተግሳጽን ተቀበልኩ አለ፥ ተማርኩ ተገሰጽኩ አለ። ስንፍና መፍረስን እንደሚያመጣ፥ ስንፍና ዋጋን ስራን እንደሚያጠፋ ተማረ። አካባቢያችን የከሰረ ቢዝነስ አለ? ለምን? የፈረሰ ትዳር አለ? ለምንድነው የፈረሰው? 

የእግዚአብሔር ቃል የተጻፈልን ለትምህርታችን እንደመሆኑ መጠን፥ ዛሬ በማለዳ ሳነብ በነበረው በኢሳይያስ መጽሐፍ ምእራፍ አንድ ላይ ከነበሩት የእስራኤል ሕዝቦች ሕይወት መፍረስ አንድ ትልቅ ነገር ተማርኩ። ምእራፉ እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ በሕይወታቸው መፍረስ ምክኒያት የወቀሰበት ምእራፍ ነው። የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔር እንዲያደርጉ ያዘዛቸውን መስዋእቶች፣ መባቻና በዓላቶች በሙሉ በማድረግ ላይ የነበሩበት፥ ነገር ግን ሕይወታቸው በብዙ እግዚአብሔርን በሚያሳዝን ድርጊቶች የተሞላበት ጊዜ ነበር። ሕዝቡ መስዋእቶችን ለማቅረብ እንዲሁም እግዚአብሔር እንዲያደርጉ ያዘዛቸውን ባእላቶች እና መባቻዎች በማድረግ ይተጋሉ፥ ነገር ግን ሕይወታቸው ክፋትን በማድረግ፣ ደምን በማፍሰስ እና እግዚአብሔርን በመበደል የተሞላ ነበር። ከዚህም የተነሳ፥ እግዚአብሔር መስዋእታቸውን መጥላቱንና መጸየፉን እንዲህ በማለት ከቁጥር 10 ጀምሮ ይነግራቸዋል። 

“እናንተ የሰዶም አለቆች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እናንተ የገሞራ ሕዝብ ሆይ፥ የአምላካችንን ሕግ አድምጡ። የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለእኔ ምን ይጠቅመኛል? ይላል እግዚአብሔር፤ የሚቃጠለውን የአውራ በግ መሥዋዕትንና የፍሪዳን ስብ ጠግቤያለሁ፤ የበሬና የበግ ጠቦት የአውራ ፍየልም ደም ደስ አያሰኘኝም። በእኔ ፊት ልትታዩ ብትመጡ ይህን የመቅደሴን አደባባይ መርገጣችሁን ከእጃችሁ የሚሻ ማን ነው? ምናምንቴውን ቍርባን ጨምራችሁ አታምጡ፤ ዕጣን በእኔ ዘንድ አጸያፊ ነው፤ መባቻችሁንና ሰንበታችሁን በጉባኤ መሰብሰባችሁን አልወድድም፤ በደልንም የተቀደሰውንም ጉባኤ አልታገሥም። መባቻችሁንና በዓላቶቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች፤ ሸክም ሆነውብኛል፥ ልታገሣቸውም ደክሜያለሁ። እጃችሁንም ወደ እኔ ብትዘረጉ ዓይኔን ከእናንተ እሰውራለሁ፥ ልመናንም ብታበዙ አልሰማችሁም፤ እጆቻችሁ ደም ተሞልተዋል።“ 

በማለት እግዚአብሔር ሕዝቡን ይወቅሳል። “የመስዋእታችሁ ብዛት ለእኔ ምን ይጠቅመኛል” ብሎ እግዚአብሔር እስከሚናገራቸው ድረስ፥ ሕዝቡ ብዙ መስዋእትን በእግዚአብሔር ፊት ያመጡ ነበር። መስዋእት በማቅረብ ጎበዞች ናቸው፥ ይተጋሉ። በመሰብሰብና በአላቶችን በማክበር ጎበዞች ናቸው ይተጋሉ። ነገር ግን ሕይወት ጎሏቸው ነበር፥ ኑሮ ጎሏቸው ነበር። ከዚህም የተነሳ ምንም መስዋእታቸው በእግዚአብሔር ፊት ቢበዛም፥ በመስዋእታቸው ብዛት እግዚአብሔር ደስ ሊሰኝ አልቻለም። እንዲያውም ጭራሽ እግዚአብሔር ምን ሲላቸው እንመለከታለን፥ “ቁርባንና እጣናችሁ በፊቴ አስጸያፊ ሆነ፥ መባቻችሁን ሰንበታችሁን እና በጉባኤ መሰብሰባችሁን አልወደውም፥ በደላችሁን ልታገስ አልችልም። የምታደርጉልኝን መባቻና በዓል ነፍሴ ጠላችው ጭራሽ ሸክም ሆነብኝ፥ መታገስ ደከምኩ ስለዚህ ልመናችሁን አልሰማም እጃችሁንም ወደ እኔ ብታነሱ አላያችሁም ምክኒያቱም እጆቻችሁ በደም ተሞልተዋል። ኑና እንዋቀስ  መስዋእቱን ለጊዜው ተውትና እስኪ እጃችሁን ታጠቡ፥ ሰውነታችሁንም አንጹ የስራችሁን ክፋት አስወግዱ፥ መልካም ማድረግን ተማሩ ፍርድን ፈልጉ፥ የተገፋውን አድኑ፥ ለድሀ አደጉ ፍረዱለት ስለ መበለቲቱም ተምዋገቱ። በፊቴ እውነተኛ ንሰሀ ግቡ እያለ ይናገራቸዋል።” “ኑና እንዋቀስ” አለ እግዚአብሔር ሕዝቡን “ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደ አመዳይ ትነጻለች፤ እንደ ደምም ብትቀላ እንደ ባዘቶ ትጠራለች። እሺ ብላችሁ ከታዘዛችሁ የምድርን በረከት በሙሉ ትበላላችሁ፥ እምቢ ካላችሁ ግን ሰይፍ ይበላችሁዋል።” እያለ እግዚአብሔር ሕዝቡን የወቀሰበት የእግዚአብሔር ቃል ክፍል ነው። 

ይሄ የእግዚአብሔር ቃል ክፍል አንድ ነገር ያስታውሰኛል። እኔ በማመልክበት ቤተክርስቲያን ውስጥ ባለኝ የአገልግሎት ክፍል ሊያስተምረን ከኢትዮጲያ የመጣ አንድ የማከብረው አገልጋይ ከአመታቶች በፊት የነገረን አንድ ነገር ነበር። ይሄ አገልጋይ እንዲህ አለ። “እግዚአብሔር መስዋእትን የሚቀበለው፥ የመስዋእት አቅራቢውን ሕይወት ሲቀበል ብቻ ነው። የመስዋእት አቅራቢውን ሕይወት ከተቀበለ፥ መስዋእቱንም ይቀበላል። የመስዋእት አቅራቢውን ሕይወት ካልተቀበለ፥ መስዋእቱንም አይቀበልም” በማለት ያስተማረን ትምህርት ልቤ ውስጥ ቀርቷል። ብዙ ጊዜ ጭንቀታችን መስዋእቱን ማቅረብ ላይ ነው። እናመልካለን፣ እንጸልያለን፣ መባ እና መስዋእታችንን እንሰጣለን። ይሄ ሁሉ መልካም ነው እንዲያውም አድርጉ ተብለን በእግዚአብሔር ቃል ላይ የታዘዝነው ትእዛዝ ነው። ነገር ግን ብዙ ጊዜ አላማችን ህብረቶች ላይ መስዋእቱን አቅርበን መሄዳችን ላይ ነው እንጂ፥ እውነተኛው መስዋእት ከሰኞች እስከ ቅዳሜ ያለው ሕይወታችን እንደሆነ አናስተውልም። መጀመሪያ እግዚአብሔር የሚቀበለው የእሁዱን አምልኮ እና መስዋእት አይደለም። መጀመሪያ የሚቀበለው ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ያለውን ሕይወታችንን ነው። 

ልክ እንደ ትምህርት ቤት ነው። አንድ ክላስ ስንወስድ ክላሱ ውስጥ የሚሰጡትን ሌክቸሮች ተከታትለን ካልተማርን፥ መጨረሻ ላይ ፈተናው ላይ መውደቃችን አይቀርም። ሕይወታችንን እንደ እግዚአብሔር ቃል እና እንደ እርሱ ፈቃድ ካልተከታተልነው መስዋእት ማቅረቡ ላይ መውደቃችን አይቀርም። ፈተናውን በጣም በጥሩ ውጤት እንድናልፍ የሚያደርገን፥ ፈተናው ቀን ላይ መገኘታችን አይደለም። ትምህርቱ በሚሰጥበት ቀናቶች መገኘታችን እና ትምህርቱ ውስጥ ያለውን ሀሳብ በአግባቡ መረዳታችን ነው። ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ወይንም የህብረት ፕሮግራም በሌለ ጊዜ ለእግዚአብሔር ህግና ስርአት የሚገዛ ሕይወት ከሌለን፥ የሚታዘዝ ሕይወት ከሌለን፣ ልክ እንደ እስራኤል ሕዝብ ሰው ባንገልም ግን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በመጥላት ከዋልን እና ካደርን የእግዚአብሔር ቃል እንደሚነግረን ወንድሙን የሚጠላ ነፍሰ ገዳይ ነውና እግዚአብሔር ከወቀሳቸው ከእስራኤል ሕዝብ የተለየ ሕይወት የለንም። በጥላቻ፣ በቂም፣ በክፋት፣ በአመጽ ውስጥ እየተመላለስን የቤተክርስቲያን ህብረቶች ላይ መጥተን ለእግዚአብሔር የምስጋናም ሆነ የዝማሬ መስዋእት እንሰዋ ማለታችን ጊዜ ከማቃጠል በስተቀር ለእኛም ሆነ ለአምላካችን ምንም የሚያመጣው ጥቅም የለም። እግዚአብሔር የመስዋእት እጥረት የለበትም። እንዲያውም መስዋእት ለማቅረብ እርሱን ለማምለክ እና ለእርሱ ለመዘመር እድል ሰጥቶን እንጂ ሰማይና ምድር ሳይሰሩ፣ የሰው ልጅ ሳይፈጠር፣ ምድር ሳትመሰረት፥ ምስጋና ሞልቶ የተረፈው አምላክ ነው። ብዙ ክብር የተረፈው አምላክ ነው። ጎሎት ስለማያውቅ አኛ አንሞላለትም። ስናመልከውም ስለሚገባው ነው እንጂ  እርሱን እየጠቀምነው ወይንም ውለታ እየሰራንለት አይደለም። ሁልጊዜ መረዳት ያለብን፥ ዋና መስዋእት ሕይወት እንጂ ዝማሬ አለመሆኑን፥ አምልኮ ኑሮ እንጂ መዝሙር እና የህብረት ስርአቶች ብቻ አለመሆናቸውን ነው። አምልኮ የሚለውን ቃል ስናስብ፥ ስለ መዝሙር ብቻ ከሚያስብ ጠባብ አስተሳሰብ መውጣት አለብን። አምልኮ ስንል በአጠቃላይ ለእግዚአብሔር ቃል ያለን መገዛት እና የመታዘዝ ሕይወት ነው። አምልኮ ትእዛዛቱን ማክበር እና መጠበቅ ነው፡፡ እርሱን በፍጹም ልባችን መውደድ እንዲሁም ሰዎችን ሁሉ እንደራሳችን መውደዳችን ነው። በፍቅር መመላለሳችን፣ በይቅርታ መመላለሳችን፣ በትጋት እና በንጹህ ሕይወት መሄዳችን ነው አምልኮ። 

በኢያሱ መጽሐፍ ምእራፍ 22 ላይ የእግዚአብሔርን ሰው ኢያሱ የሮቤልና የጋድን ልጆች እንዲሁም የምናሴ ነገድ እኩሌታ የሆኑትን ህዝብ ወደ ገዛ ርስታቸው ሊያሰናብታቸው ሲል ያላቸው የመጨረሻ ቃል ይሄ ነበር። “ብቻ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ያዘዛችሁን ትእዛዙንና ሕጉን ታደርጉ ዘንድ፥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትወድዱ ዘንድ፥ መንገዱንም ሁሉ ትሄዱ ዘንድ፥ ትእዛዙንም ትጠብቁ ዘንድ፥ ከእርሱም ጋር ትጠጉ ዘንድ፥ በፍጹምም ልባችሁ በፍጹምም ነፍሳችሁ ታመልኩ ዘንድ እጅግ ተጠንቀቁ።” አላቸው። ኢያሱ ሕዝቡን ምን አለ? እግዚአብሔርን ለማምለክ ተጠንቀቁ አላቸው። ምን በማድረግ አምልኩት አለ?፥ ያዘዛችሁን ትእዛዙንና ሕጉን በማድረግ፣ እርሱን በመውደድ፣ በመንገዱ ሁሉ በመሄድ፣ ትእዛዙን በመጠበቅ እና ከእርሱ ጋር በመጠጋት በፍጹም ልባችሁ በፍጹምም ነፍሳችሁ ታመልኩ ዘንድ ተጠንቀቁ አለ። እዚህ ኢያሱ በተናገረው የአምልኮ ዝርዝር ውስጥ ዝማሬ እና በህብረት ውስጥ የምናደርጋቸው የመስዋእት ዝርዝሮች የሉም። እዚህ ኢያሱ ሕዝቡን ባዘዘበት የአምልኮ ትእዛዝ ውስጥ የምናየው፥ ሰው ለእግዚአብሔር ቃል ያለውን መገዛት እና በቀን ለቀን ኑⶂአችን ውስጥ እንዴት ሕግና ስርዓቱን ተግባራዊ እንደምናደርግ ነው። እውነተኛ አምልኮ ለእግዚአብሔርና ለቃሉ ያለን መገዛት ነው። ህግና ስርአቱን ለመጠበቅ ዋጋ የሚከፍለው ሕይወታችን ነው። ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ወይንም ከህብረቶች ውጪ ባለው ሕይወታችን ውስጥ ለእግዚአብሔር ቃል ያለን ታማኝነት ነው። 

ይሄ ሲሆን እግዚአብሔር ሕይወታችንን ይቀበለዋል። ሕይወታችንን ሲቀበል ደግሞ የአምልኮ መስዋእታችንን ይቀበለዋል፥ ይወስደዋል፥ ያሸተዋል። “እግዚአብሔር ወደ አቤል እና ወደ መስዋእቱ ተመለከተ” እንደሚለው እግዚአብሔር መጀመሪያ ከመስዋእቱ በፊት ወደ አቤል ነው የተመለከተው። ወደ ሕይወቱ፣ ወደ አካሄዱ መስዋእቱን ይዞ ወደ መጣበት ልብ ነው የተመለከተው። ወደ ቃየን እና ወደ መስዋእቱ ግን አልተመለከተም። እግዚአብሔር መመልከት የማይፈልገው ሕይወት ካለን፥ እንዴት ነው መመልከት የሚፈልገው መስዋእት የሚኖረን? አንዳንድ ጊዜ እኮ የዝማሬ አምልኮ አይደለም የሚያስፈልገን፥ ወደ ህግና ስርአቱ ለመመለስ የወሰነ ልብና እውነተኛ ንሰሀ ነው የሚያስፈልገን። አንዳንድ ጊዜ እኮ ወርሺፕ ናይት ወይንም የአምልኮ ምሽት አይደለም የሚያስፈልገን፥ የንሰሀ እና የመመለስ ምሽት ነው የሚያስፈልገን። አንዳንዴ እኮ ምስጋናና እና ዝማሬ አይደለም የሚያስፈልገን፥ እውነተኛ የሆነ የመንፈስ ቅዱስ ወቀሳ ነው የሚያስፈልገን። ሰዎችን በሁኔታዎቻችን በንግግሮቻችን ማታለልና ማስመሰል እንችል ይሆናል። ከእግዚአብሔር አይኖች የሚከልለን አምልኮም፣ ንግግርም፣ ማስመሰልም የለም። አይኖቹ ዛሬና ትላንቶቻችንን እንዲሁም ዘላለማችንን፣ ከንግግራችን ያለፈ ልባችንን ከአለባበስ ያለፈ ነፍሳችን ውስጥ ያለውን ስሜትና ፈቃድ የሚመረምሩ ናቸው። እውነት ግን ደስ ታሰኘዋለች፥ ንጽህና ትማርከዋለች፥ ትህትና ትስበዋለች፥ እውነተኛ ንሰሀ ልቡን ታራራዋለች።

ጊዜ

ጊዜ

ጤንነት

ጤንነት