ስራ
መቼም ለመዳናችን አንዳች ነገር አለማዋጣታችን እና እንዲሁ በጸጋ መዳናችን የሚገርም እና የሚደንቅ፥ የምንጊዜውም የልባችን ምስጋና፥ ሁልጊዜ ልባችን በእግዚአብሔር ፊት አመስጋኝ የሚሆንበት እውነት ነው። ደግሞ እኮ ትንሽ እንኳን ጽድቅ ተገኝቶብን ቢሆን ቅዱስ መጽሐፉም ለጻድቅ ሰው የሚሞት በጭንቅ ሊገኝ ይችላል እንደሚለው ነው። ለእንደ እኛ አይነት ሀጢያተኞች እና ተስፋ ለሌላቸው ሰዎች የሚሞት ግን በፍጹም አይገኝም። መቼም መዳን ፍጹም የሆነ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። ሙታን የነበርነውን ሰዎች በፍቅሩ ሕያዋን ያደረገበት፣ የፍቅርን ሀይል መጨረሻው ጥጉን ያየንበት፣ እኛ ፍቅር ብለን ከምንጠራው ስሜት አልፎ ነፍሱን በመስጠት ድርጊቱ የፍቅርን ትርጉም እውነተኛ እና አይተን የማናውቀው ደረጃ ያደረሰበት፥ ከዚህ በፊት በአለም ተሰምቶም፣ ታይቶም ተደርጎም ያልታወቀ ፥ ከዚህም በኋላ የማይደረግ የአምላክ ጥበብ የተገለጠበት እጅግ በጣም አስደናቂ የሆነ ክስተት ነው። ምክኒያቱም ስለ ቀድሞ ታሪካችን ሲናገር፥ ከፍጥረታችሁ የቁጣ ልጆች ነበራችሁ፥ በበደላችሁና በሀጢያታችሁ ሙታን ነበራችሁ የተባልንበት ሙታን ሰፈር የእግዚአብሔር ፍቅር ሲመጣ፥ ምንም ተስፋ በሌለበት ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የነበረ ሕዝብ ታላቅ እና አስደናቂ ብርሀን ሲያይ፥ ባሪያ ልጅ ተብሎ ያለፋበትን መንግስት ሲወርስ ቃላቶች መግለጥ ከሚችሉት በላይ ይደንቃል። ልክ እንደ አስቴር እኮ ነው የሆነው። ንጉሱ አስቴርን ስለወደዳት ብቻ ያለፋችበትን፣ ያላዋቀረችውን እና ያልደከመችበትን መንግስት እኩሌታውን እራሱ ቢሆን ጠይቂኝ ያስባለው እኮ ንጉሱ እሷን የወደደበት ፍቅር ብቻ ነው። እኛም ያለፋንበትን መንግስት ወራሾች የሆነው፥ እንዲሁ ስለወደደን ብቻ እንጂ ከእኛ ውስጥ አንዳችንም የተገባን ሆነን አይደለም። የእግዚአብሔርን ፍቅር፥ መንፈስ ቅዱስ እራሱ ለነፍሳችን ካላስረዳልን ልክ እንደ ሂሳብ አንድና አንድ ብለን በስጋ አይምሮአችን መረዳት እና መገመት የምንችለው ነገር አይደለም። ኢየሱስ አንድ ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ ያላቸው ነገር ትዝ አለኝ። በዮሐንስ ወንጌል መጽሐፍ ላይ እንዲህ አላቸው። “የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፥ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፥ የሚመጣውንም ይነግራችኋል” አላቸው። አይገርምም ኢየሱስ በጊዜው ብዙ ነገሮችን ሊነግራቸው ቢፈልግም፥ ሊነግራችው የወደደውን ብዙ ነገር መሸከም የሚችሉበት አቅም አልነበራቸውም። የእግዚአብሔርን እውነት ለመሸከም እና ለመረዳት የእግዚአብሔር መንፈስ ያስፈልጋቸው ነበር።
እግዚአብሔር ልጁን ያውም አንድያ ልጁን ለዚያ አሰቃቂ የመስቀል ሞት መስጠቱ፥ ሰዎች ከዘላለም ሞት እና ጥፋት እንዲድኑ የፈለገበትን ከፍተኛ የፍላጎት መጠን ያመለክታል። ከእኛ ጥፋት ልጁን በሞት ውስጥ ማሳለፍን መረጠ። አሁንም ቢሆን ሰዎች ሁሉ እንዲድኑ ወዶ ስለ ሰዎች መዳን ይታገሳል። አምላክ መቼም ደግ ነው፥ በጣም ደግ ነው። ከዚህ በላይ ደግ መሆን አይችልም። ደግነቱን፣ መልካምነቱን፣ ፍቅሩን፣ ምህረቱን ሁሉ አንድ ላይ አርጎ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ አሳይቷል። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ምህረት ማሳያ፣ የፍቅሩ መገለጫ፣ የመልካምነቱ ምልክት፥ የደግነቱ ምስክር ነው። እግዚአብሔር መልካም ነው እንዴ? ከተባለ፥ ይኸው ምልክቱ፥ የእግዚአብሔር መልካምነትና ፍቅር በተግባር የተገለጠበት ማረጋገጫ ምልክቱ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ታዲያ በእምነት ብቻ ያገኘነውን ይሄ ሁሉ ዘለዓለማዊ የሆነ የሕይወት በረከት እንዴት እንደ ቀላል ነገር እናየዋለን? በሰዎች “አታካብዱ ወይንም አትመናፈሱ” መባልን ፈርተን እንዴት ዝም ብሎ ተራ የሆነ ሕይወት እንኖራለን? እስከ ጥግ ሄዶ ለሞተልን አምላክ፥ እስከ ጥግ በቻልነው ሁሉ መኖር ነው እንጂ። በሰዎች ፊት እርቃኑን መስቀል ላይ ለዋለልን አምላክ፥ ማካበድም ከሆነ ማካበድ ነው እንጂ። ደግሞ ለእግዚአብሔር ያልተካበደ ሌላ ለማን ይካበዳል? ለእግዚአብሔር ያልሆነ ሕይወትስ ሌላ ለማን ይሆናል? ይሄንን ሁሉ ዋጋ ከፍሎ የወደደን እና የሞተልን ይሄ አምላክ ደግሞ፥ እኛም ሁለንተናችንን ሰጥተን እስከ ጥግ ድረስ ስንወደውና ስንኖርለት ይደሰታል። በቃ እግዚአብሔር ነካ ነካ የሆነ ከላይ ከላይ የሆነ ነገር፣ እንዲያው ለነገሩ የሆነ ነገር አይመቸውም። ሙሉ ልባችንን ይፈልጋል፣ ሙሉ መሰጠታችንን ይጠይቃል፣ ሁለንተናችንን ይፈልጋል። በእውነተኛ እና ለእርሱ ዋጋ በሚከፍል ሕይወታችን ይደሰታል።
መዳን እኛ ሳንለፋበት በእምነት ብቻ የተቀበልነው ሕይወት ሲሆን፥ ይሄ ያመንነው እምነት ግን አምኛለሁ ከሚል ቃል አልፎ በስራ እና በተግባር የሚገለጥ መሆኑን የእግዚአብሔር ቃል በግልጥ ይናገራል። እምነት በስራ እና በድርጊት የሚገለጥ ነገር ነው። ያመነ ሰው ያመነውን፥ ያመነበትን ሕይወት ነው የሚኖረው። ለምሳሌ አንድን ሰው ለአንድ ሳምንት ቤቱ ሄዳችሁ ጥናት አድርጉበት ወይንም ገምግሙት ተብሎ ቢነገረን እና ሰውዬው ስለ ራሱ ምንም ነገር ባይነግረን፥ በየቀኑ የሚያደርጋቸውን ነገሮች በማየት እምነቱን በትክክል ማወቅ እንችላለን። ይሄ ልንገመግመው የሄድነው ሰው በመስራት የሚያምን ሰው ከሆነ፥ በየቀኑ ተነስቶ በሰአቱ ስራ ሲሄድ እናየዋለን፥ ለምሳሌ በእስፖርት የሚያምን ሰው ከሆነ፥ ጂም ሲሄድ እና እስትፓርት ሲሰራ እናየዋለን፥ ጤንነቱን መጠበቅ እንዳለበት የሚያምን ሰው ከሆነ፥ ጤናማ ምግቦችን እየመረጠ ሲመገብ እናየዋለን፥ ገንዘቡን የሚቆጥብ ከሆነ፥ ሴቭ በማድረግ የሚያምን ነው እንደሆነ እንረዳለን። ስለ እምነቱ ሰውዬው ቃል ሳይናገር፥ ድርጊቶቹን ብቻ በመመልከት ልቡና እምነቱ ያለበትን ቦታ እንዲሁ መረዳት እና ማወቅ እንችላለን። ድርጊቶቹ በሙሉ እምነቶቹን የሚያመለክቱ ናቸው። ለምሳሌ ግን አንድ ሰው በመስራት አምናለሁ ብሎ እየተናገረ፥ ያለ ምንም ምክኒያት ስራውን እየተወ ቁጭ ብሎ ከዋለ፥ ይሄ ሰው በመስራት አምናለሁ ይላል እንጂ በመስራት አያምንም። እምነት እና ስራ የተለያዩ ነገሮች ሳይሆኑ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች መሆናቸውን የያእቆብ መልእክት ምእራፍ 1፡26 ላይ እንዲህ በማለት የእግዚአብሔር ቃል ይናገራል። “ከነፍስ የተለየ ስጋ የሞተ እንደሆነ እንዲሁ ደግሞ ከስራ የተለየ እምነት የሞተ ነው” ይላል። በክርስቶስ አምናለሁ ያልን የዳንን ሰዎች፥ እምነታችን በድርጊቶቻችን ውስጥ ካልተገለጠ ወይንም እግዚአብሔር የጠራንን ሕይወት ካልኖርን ወይንም ቢያንስ ለመኖር ካልሞከርን የቱ ጋር ነው ያመነው? የተጠራነው እኮ ልዩ የሆነ ሕይወት እንድንኖር ነው። ለምሳሌ ኢትዮጲያ እንኖር በነበረ ሰአት የምንተዳደረው በኢትዮጲያ ህገ መንግስት ነበር። ልክ እዚህ ሀገር ከመጣንበት ጊዜ ጀምሮ ግን ሙሉ በሙሉ የመንግስት ለውጥ ነው ያደረግነው። የሕገ መንግስት ለውጥ ነው ያደረግነው። አሁን እኛ ከኢትዮጲያ ውጪ የምንኖር ሰዎች፥ በኢትዮጲያ መንግስት አይደለም የምንተዳደረው። ከኢትዮጲያ ልዩ በሆነ መንግስት ስር ነን። የምንሆነው፥ የምንኖርበት ሀገር ባወጣው ህገ መንግስት ነው። እዚህ ሀገር ላይ ለመቆየት ከመረጥን፥ ህገ መንግስቱን መቀበል እና ተግባራዊ ማድረግ መብታችን ሳይሆን ግዴታችን ነው። እንዲያውም ከኢትዮጲያ ሀገር ወጥተን የሌላ ሀገር ዜጋ ለመሆን ዜግነት ስንጠይቅ እኮ፥ እጃችንን አንስተን ቃል እንድንገባ ያረጉናል። ህገ መንግስታቸውን እንድናከብር፥ ሀገራቸውን እንድንወድ እና እንድንጠብቅ። ጌታን ስንቀበል የህገ መንግስት ለውጥ ነው ያደረግነው። አዲስ መንግስት፣ አዲስ የሕይወት አካሄድ፣ አዲስ እርምጃ፣ አዲስ ኪዳን እና አዲስ ሕይወት። አሁን በዚህች አለም መንግስት አይደለም የምንተዳደረው፥ ለሰማያዊው መንግስት ዜግነት ጠይቀን ቃል ገብተን ዜጎች ሆነናል። የምንተዳደረው በድሮው መንግስት ስርዓት አይደለም። ዜግነት ባገኘንበት ሀገር ሕገ መንግስት ነው። ሕገ መንግስቱ ፈጽሞ ጨለማ ከሆነው እና ከኋላ ትተን ከመጣንበት ከዚህች አለም መንግስት የተለየ ነው፡፡ ፈጽሞ የተለየ የብርሀን መንግስት ነው። ይሄ መንግስት የቅድስና መንግስት ነው። በመንፈስ ቅዱስ ኋይል እየተሞላን የድሮውን መንግስት ስራ በመተው እንዲሁም ስጋን እና ምኞቱን በመካድ ቅድስናን ተግባራዊ የምናረግበት፥ በድርጊቶቻችን በንግግሮቻችን በሀሳቦቻችን ሁሉ ሁለንተናችንን ሕያው እና ቅዱስ መስዋእት እያደረግን ለአምላካችን የምናቀርብበት፥ የሚጠሉንን ሁሉ የምንወድበት፣ የሚረግሙንን የምንመርቅበት፣ ለሚያሳድዱን እና ክፉ ስለሚያረጉብን ሰዎች የምንጸልይበት። የክርስቶስ ሕያው መንፈስ በእኛ ውስጥ አድሮ ፍሬ በማፍራት የክርስቶስን አይነት ሕይወት ለመኖር እርዳታን የምናገኝበት አስደናቂ መንግስት ነው።
ያዳነን ጸጋ እራሱ በዚያኛው ትተን በመጣንበት መንግስት ውስጥ ያለውን ሀጢያተኝነትን እና አለማዊ ምኞት ክደን ራሳችንን እየገዛን፣ በልክ እየኖርን፣ በጽድቅ እና እግዚአብሔርን በመምሰል መኖርን እየተማርን የአምላካችንን እና የመድሀኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እንድንጠባበቅ የሚረዳን ጸጋ ነው። በ2ኛ ጴጥሮስ 1፡5 ላይ ሲናገር ካመናችሁ በኋላ በእምነታችሁ ላይ በጎነትን ጨምሩ፣ በበጎነታችሁ ላይ ደግሞ እውቀትን ጨምሩ፥ በእውቀት ላይ ደግሞ ራስን መግዛትን ጨምሩ፥ እራሳችሁን እየገዛችሁ ደግሞ መጽናትን ጨምሩ፥ በዚያ ላይ ደግሞ እግዚአብሔርን መምሰልን ጨምሩ፥ እግዚአብሔርን እየመሰላችሁ የወንድማማቾችን መዋደድ ጨምራችሁ በዚያ ላይ ፍቅርን ጨምሩ እነዚህን ነገሮች በማድረግ ትጋትን አሳዩ በማለት ጴጥሮስ በጻፈው ጽሁፍ ውስጥ ይመክራል። ይሄንን የ2ኛ ጴጥሮስ መጽሐፍ ምእራፍ አንድን እያነበብኩ ቁጥር 10ን በማስተዋል ሆኜ ሳነበው ደነገጥኩ። እንዲህ ይላል፥ “ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ፤ እነዚህን ብታደርጉ ከቶ አትሰናከሉምና።” ይላል። አያችሁ ሁላችንም ተጠርተናል፥ ሁላችንም ተመርጠናል ግን ጴጥሮስ የሚነግረን ወሳኝ ነገር ይሄ ነው። መጠራታችንን እና መመረጣችንን የምናጸናው የእግዚአብሔርን ፈቃድ እያደረግን በመትጋት ነው። የእስራኤልን ሕዝብ ጥሪና የምድረበዳ ጉዞ ስንመለከት፥ ወደ ከነአን ለመግባት ተስፋ የተሰጣቸው የተጠሩት እና የተመረጡት እኮ ሁሉም የእስራኤል ሕዝብ ነበሩ። ነገር ግን መንገድ ላይ፥ ምድረበዳ ላይ የቀሩ ብዙ ሰዎች ነበሩ። የሕዝቡ ምድረበዳ ላይ መቅረት ችግሩ የእግዚአብሔር አይደለም። እግዚአብሔርማ እኮ በጸናች እጅ በበረታች ክንድ ስንት አመት ሙሉ ከተገዙበት ጽኑ ከሆነ ባርነት አውጥቷቸዋል። በግብጽ ምድር ለሕዝቡ ተዋጊ ሆኗል፥ ባህሩን ወደ ደም ቀይሮ፥ የግብጽን በኩር በሙሉ ገሎ፥ በምድሪቱ ላይ ፍርሀት እና ድንጋጤን አምጥቶ ለሕዝቡ ተዋግቷል። እግዚአብሔርማ በድንቅና በተአምራት በግርማና በብዙ ሞገስ በማውጣት፥ አስጨናቂዎቻቸውን በባህር ውስጥ ጥሎ፥ ጠላቶቻቸውን አዋርዶ ለዘለዓለም እንዳያይዋቸው አርጎ ሕዝቡን አድኗል። ይሄ ምን ያሳየናል፥ እግዚአብሔር ህዝቡን ነጻ ለማውጣት እና ተስፋ ወደገባላቸው ምድር ለማስገባት የነበረውን ብርቱ ፍላጎት ያሳያል። ነገር ግን ወደ ተስፋይቱ ምድር የገቡት፥ እግዚአብሔርን በማመን ህግና ትእዛዙን በማድረግ ፈጽመው የተከተሉት ኢያሱ እና ካሌብ ብቻ ነበሩ። ሌሎቹ የገቡት ምድረበዳ ላይ የተወለዱት ልጆች ብቻ እንጂ፥ ተስፋውን ሰምተው ከግብጽ ከወጡት ውስጥ እኮ ከሁለቱ ከኢያሱና ከካሌብ በስተቀር የገባ ሌላ ሰው አልነበረም። ይሄ እንግዲህ ቆም ብለን እንድናስብ ካላረገን ሌላ ምን ያቆመናል? መዳን በጸጋ ብቻ ነው በስራ አይደለም። መዳን በእምነት ብቻ ነው የእኛ ስራ የለበትም። እምነታችን ግን የሚጸናው በትጋት እግዚአብሔርን እና ቃሉን በሕይወታችን ተግባራዊ በማድረግ በተግባር ውስጥ ነው። አምናለሁ እያልን ሌላ ከእምነታችን ጋር የማይገናኝ ሕይወት ከኖርን አምነናል አልን እንጂ አላመንም ምክኒያቱ ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል እምነት እና ስራን፥ እምነት እና ሕይወትን ለያይቶ ስለማያያቸው ነው።