Hi.

Welcome to my site! I hope and pray that the blogs I post encourages and uplifts you to keep building a deeper relationship with the Lord.

God bless you!

ጊዜ

ጊዜ

መስራት የምፈልጋቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ጊዜዬንና ሰአቴን የሚፈልጉ ብዙ ነገሮች ህይወቴ ላይ አሉ። በአንዱ ነገር ውስድ እልና ሌሎቹን ህይወቴ ላይ ያሉ አስፈላጊ ነገሮች ችላ ስላቸው እራሴን አገኘዋለሁ። ከዚያ ደግሞ ሀላፊነቶቼን በትክክል እየተወጣሁ እንዳልሆነ አስቤ አዝናለሁ። በዚህ የህይወት ጎዳና ውስጥ እያለሁ ነው አንድ ቀን ወረቀትና እስክሪፕቶ አውጥቼ በህይወቴ ላይ በጣም አስፈላጊና ጊዜዬ ይገባቸዋል የምላቸውን ነገሮች በዝርዝር ለመጻፍ ውስጤ የተመራው። አንደኛ ሁለተኛ ሶስተኛ እያልኩ ዝርዝሮቹን በሙሉ ጻፍኩ። ከዚያ ደግሞ ለዘረዘርኳቸው ነገሮች በሙሉ በሳምንቴ ውስጥ ምን ያህል ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው ዘርዝሬ ጻፍኩ። ከዚያ እነዚህን ነገሮች በቀናቶቼ ውስጥ በምን በምን ሰአት ውስጥ እንደማደርጋቸው ውሳኔ ከሰጠሁ በኋላ እግዚአብሄር በረዳኝ መጠን ውሳኔዬን ተከትዬ ለነገሮቹ በሰጠኋቸው ጊዜያቶች ውስጥ መመራት ስጀምር፥ ውጤቱን በጣም ወደድኩት። ህይወቴ ሚዛናዊነቱን እየጠበቀ፣ ሀላፊነቶቼ በሙሉ የሚገባቸውን ጊዜና ትኩረት እያገኙ ስለመጡ በጊዜዬ አጠቃቀም ደስተኛ እየሆንኩኝ መጣሁ። 

እግዚአብሄር የሰውን ፊት አይቶ እንደማያደላው ማንነቱ መጠን፥ ለሰዎች ሁሉ እኩል አርጎ ከሰጣቸው ስጦታዎች ውስጥ አንዱ ነው ጊዜ። ሀብታሙም ደሀውም፣ ወንዱም ሴቱም፣ ትልቁም ትንሹም፣ የተማረውም ያልተማረውም እግዚአብሄር በየቀኑ ከሰጠው የ24 ሰአት ስጦታ አልጎደለም። ለሁሉም እኩል የተሰጠ ስጦታ ይሁን እንጂ ግን ሰው ሁሉ ጊዜን የሚያይበት መንገድ የተለያየ ነው። ለአንዳንዱ በሰአትና በደቂቃ ከፋፍሎ ያሰበውን ሁሉ የሚያሳካበት፣ እቅድና ምኞቶቹን እውን የሚያረግበት የስኬት መንገዱ ነው። ለሌላው ደግሞ ወደ ጎን ጠጋ ብሎ ቆሞ፥ እለፍ እለፍ ጠጋ ልበልልህ እያለ ቆሞ የሚያሳልፈው ተራ ነገሩ ነው። ኸረ ቆይ እንደውም ጊዜው ትንሽ ቆየት ቢልም አንድ ቃለ ምልልስ እየሰማሁ እግዜር ማስተዋል የሰጠው ታዳጊ ወጣት ጊዜን ሲያብራራ ያለውን ልንገራችሁ። በዚህ ምድር ላይ ሶስት አይነት ሰዎች አሉ አለ። የመጀመሪያዎቹ ጊዜን የሚጠቀሙ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ጊዜ ውስጥ ያለው ውድነት የገባቸው፣ እቅድና ፕሮግራም እያወጡ የሚሰሩ ናቸው። መነሻና መድረሻ ያላቸው እንዲሁም ምን ማድረግ እንደሚፈልጉ የሚያውቁ ሰዎች ናቸው። ሁለተኞቹ ደግሞ ጊዜ የሚጠቀምባቸው ሰዎች ናቸው። እነዚህ ምንም እቅድና ፕሮግራም ስለሌላቸው ጊዜው ካመጣው ነገር ሁሉ ጋር አብረው የሚሄዱ፣ ቀናቸው ላይ ኑ ካላቸው ነገር ሁሉ ጋር አብረው የሚሄዱ ናቸው። ሶስተኞቹ ሰዎች ደግሞ ጊዜን የሚያሳልፉ ናቸው። እነዚህ የነ ፌስ ቡክ ወዳጆች፣ ጊዜን በምን ልጠቀመው ብለው ጊዜን ስለመጠቀም ሳይሆን ጊዜን ስለማሳለፍ የሚጨነቁ ሰዎች ናቸው ብሎ የገለጸው ነገር ሁሌ ትዝ ይለኛል። እናንተ ጊዜን እንዴት ነው የምታዩት? እኔ ጊዜን ሳስብ ቶሎ ብሎ ወደ ሀሳቤ የሚመጣው ዘላለም ነው። ብዙ በህይወት አውቃቸው የነበሩ ዛሬ ግን የዚህች ምድር ጊዜያቸው አልቋል ተብለው ወደውም ሆነ ሳይወዱ ከዚህች ምድር የተሰናበቱ ሰዎችን አውቃለሁ። እነዚህ ሰዎች የሆነ ወቅት ላይ እዚህች ምድር ላይ የሚቆዩበት ጊዜ የሚባል እድል ተሰጥቷቸው የነበሩ ሰዎች ናቸው። አሁን ግን እድሉን መልሰው ቢፈልጉት እንኳን አያገኙትም። እነዚህ ሰዎች ታዲያ ተሰቷቸው በነበረው የምድር ጊዜ ያደረጓቸው ነገሮች፥ ዘላለማቸውን ላይ መልካም ወይንም መልካም ያልሆነ ተጽእኖን የሚፈጥር ነው። ሌላው ቀርቶ በኢየሱስ ክርስቶስ ድህነትን ቢያገኙም እንኳን፥ ክርስቶስን ካገኙ በኋላ ያላቸው የሕይወት አካሄድ እና በተሰጣቸው ጊዜ ያከናወኗቸው ነገሮች፥ በእግዚአብሔር ፊት የሚገመገም ነው። 

በተሰጣቸው ምድራዊ ጊዜ በብዙ ዋጋ መክፈል የእግዚአብሄርን ሀሳብ ሲኖሩና ሲያገለግሉ የነበሩ እንደ እነ ጳውሎስ ያሉ ሰዎችና ከዳኑ በኋላ እንደፈለጉ የኖሩ ሰዎች በዘላለም ውስጥ አንድ አይነት ቦታ እንደሌላቸው መጽሀፍ ቅዱሳችንም ይናገራል። እንዲያውም በጭንቅ እንደሚድኑ ይሆናሉ የሚላቸው ሰዎችም አሉ። በአንጻሩ ደግሞ በተሰጣቸው ጊዜ የእግዚአብሔርን ሐሳብ በብዙ ትጋት እና ዋጋ መክፈል ያገለገሉ ሰዎች በክብርና በዘላለማዊ ሽልማት የዘላለም ብድራታቸውን ከራሱ ከጌታ እጅ እንደሚቀበሉ ቃሉ ይናገራል። እግዚአብሄር ለዚህ ክብር ያብቃችሁ። የሆነ ደህና ስራ ሰርተን እኮ መድረክ ላይ ወጥተን በሰው ፊት መሸለም እራሱ የሆነ ስሜት ካለው፣ በብዙ መላእክቶችና ቅዱሳን ፊት በብዙ ክብር ከዘላለም አምላክ ከእግዚአብሄር እጅ ሽልማት መቀበል ምን ይመስል ይሆን? 

በምድር ላይ የተሰጠኝን ጊዜ ሳስብ፥ ዘላለምን አብሬ ስለማስብ እግዚአብሄር የሰጠኝን ውድ የጊዜ ስጦታ በአግባቡ እንድጠቀምበት ይረዳኛል። የእናንተን አላውቅም እኔ ግን የምሞትበት ቀን ላይ ምንም አይነት ቁጭት ውስጤ እንዲኖር አልፈልግም። የዛን ቀን በተሰጠኝ ጊዜ ውስጥ ስላልሰራኋቸው ነገሮች በማሰብ ጸጸት እንዲሰማኝ አልፈልግም። እንዲሰማኝ የምፈልገው ልክ ጳውሎስ ሊሞት ሲል ይሰማው የነበረው ደስታ እና እግዚአብሄርን ለማየት ያለ ጉጉት ነው። ይሄ አይነቱ ጸጸት የሌለበት መጨረሻ ሊኖረን የሚችለው ደግሞ በተሰጠን ጊዜ መስራት የሚገባንን ነገር ሰርተን ስንጨርስ ነው። 

ለምሳሌ፥ በዚህች ምድር ላይ የቀራችሁ 6 ወራቶች ብቻ ናቸው ብንባል፥ ዛሬ የምንኖረውን አይነት ኑሮ የምንኖር ይመስላችኋል? ቅድሚያ መስጠት ስላለብንና ስለሌለብን ነገሮች ደግመን የምናስብ አይመስላችሁም? እያንዳንዱን ቀን እግዚአብሄርን ከ6 ወር በኋላ እንደምናየው እያሰብን በፊቱ መቆማችንን አውቀን እርሱ ዋጋ ለሚሰጣቸው ነገሮች ዋጋ እየሰጠን እያንዳንዱን ቀናቶቻችንን ከዘላለም አንጻር የምንጠቀምባቸው አይመስላችሁም? ታዲያ ግን ለመኖር 6 ወር ብቻ እንዳልቀረን እርግጠኛ የሚያረገን ነገር ምንድነው? ምንድነው ረጅም አመታቶች እንደምንኖር የሚያስመካን? ጤነኛ መሆናችን? ጤነኛ ሆነው ይኖሩ የነበሩ ወደ ጌታ የሄዱ ሰዎችን አናውቅም? ወጣትነታችን ነው? ወጣት ሆነው እንዲያውም ከእኛ በእድሜ ያነሱ ሰዎች በድንገት ሲሄዱ አላየንም? ያለን ገንዘብ ሀብት፣ አካባቢያችን ያሉ ብዙ ወዳጆች፥ እግዚአብሔር ይወስን እንጂ እነዚህ አንዳቸውም እግዚአብሔር ከወሰነልን ቀን ሊያሳልፉን አይችሉም። እሺ እኛ ሳንሄድ ደግሞ ኢየሱስስ ድንገት ቢመጣስ? የምመጣው እንደ ሌባ ድንገት ነው ማለቱ ሁልጊዜ የተዘጋጀ ህይወት እንዲኖረንና የሰጠንን ጊዜ በአግባቡ እንድንጠቀምበት ለማሳሰብ አይመስላችሁም? 

መቼም ስለጊዜ አጠቃቀም ካነሳን፥ በዚህ ምድር ላይ የተሰጠውን ጊዜ በሙሉ በአግባቡ ተጠቅሞ እግዚአብሄርን ስላከበረው ትልቁ ምሳሌያችን ስለ ክርስቶስ ሳናነሳ ልናልፍ አንችልም። ወደ ምድር የመጣበትን አላማ ጠንቅቆ ማወቁ፣ የተሰጠውን ጊዜ በአግባቡ እንዲጠቀምበት አርጎታል። ምንም ያባከነው ጊዜ አልነበረም። ትርፍ ጊዜ አልነበረውም። መቼ ለጸሎት ጊዜ መውሰድ እንዳለበት ያውቃል፣ መቼ መስራት እንዳለበት ያውቃል፣ መቼ ወደ ምድረበዳ ሄዶ ማረፍ እንዳለበት ያውቃል፣ መቼ ማገልገል እንዳለበት ያውቃል፣ ሌላው ቢቀር መቼ ዝም ማለትና መቼ መልስ መስጠት እንዳለበት እራሱ ጠንቅቆ ያውቃል። ጊዜውን በሚገባ መጠቀሙ ብቻ ሳይሆን፣ ለሚያደርገው ለየትኛውም ነገር፥ ትክክለኛውን ጊዜ ጠንቅቆ ያውቃል። አለምን ሁሉ ከዘላለም ጥፋት የሚያድን ስራ ቢሰራም፥ ይሄንን የሰዎችን ሁሉ ዘላለም የሚቀይር ስራ ለመስራት ከ33 አመት ተኩል በላይ አልፈጀበትም። በእነዚህ አጭር አመታቶች ውስጥ የመጣበትን አላማ አሳክቶ እንዲያልፍ ከረዳው ነገሮች አንዱ፥ ጊዜውን በአግባቡ መጠቀሙና የእያንዳንዱን ነገር ጊዜ ጠንቅቆ ማወቁ ነው። ኢየሱስ በዚህች ምድር ላይ ሲመላለስ፥ የዚህች ምድር ቆይታው በጣም አጭር እንደሆነች በልቡ እያሰበ ነው። የተመላለሰው የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማድረግ የመጣበትን አላማ እያሰበ ነው። እኛስ ጊዜን እንዴት እየተጠቀምንበት ይሆን? እያንዳንዱ ቀን በእድሜያችን ላይ ሲደመር፥ በዚህች ምድር ላይ የተሰጠን የጊዜ ገድብ ለመጠናቀቅ አንድ ቀን እየቀረበ እንደሆነ ብዙ ጊዜ ማስታወስ አለብን። ጊዜን በአግባቡ ለመጠቀም ከሚረዳን ነገሮች ውስጥ ሁለት ዋና ዋና ነገሮችን በአጭሩ እናንሳ፦ 

1ኛ. በሕይወታችን ላይ ያለውን የእግዚአብሔር አላማ ማወቅ፦ መቼም ጊዜን ተጠቀምን የሚባለው በጊዜ ውስጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ስናደርግ ነው። እኛ ዘርዝሩ ብንባል አስፈላጊ ብለን የምንላቸውን ነገሮች አንድ ሁለት ሶስት እያልን እንዘረዝር ይሆናል። ነገር ግን ከዘላለም አንጻር ስንመለከተው፥ በሕይወታችን አስፈላጊ የሚባለው አንደኛው ነገር እግዚአብሔር እኛን የፈጠረበት አላማ ነው። ኢየሱስ ጊዜውን በሙሉ የሰጠው፥ ወደ ምድር ለመጣበት ወይንም እግዚአብሔር እርሱን ለላከበት አላማ ነበር። እኛስ ለምንድነው የተፈጠርነው? ምን ለማድረግ ነው የተላክነው? በዚህች ምድር ላይ በተሰጠን በዚህች ውስን ጊዜ ውስጥ እግዚአብሔር በሕይወታችን ሊያከናውን የፈለገው ዋና አላማ ምንድነው? በየትኛው አገልግሎት ውስጥ ነው የጠራኝ? በግል ሕይወቴስ ምን አደርግ ዘንድ ይፈልጋል የሚሉትን ጥያቄዎች መልስ ከእግዚአብሔር ማግኘታችን፥ ጊዜ እና ትኩረታችንን እዚያ ዋና አላማ ላይ በማድረግ በተሰጠን ጊዜ ውስጥ እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆነውን የእግዚአብሔር ሀሳብ አከናውነን እንድናልፍ ይረዳናል።

2ኛ በመንፈስ ቅዱስ መመራት፦ በዚህች ምድር ላይ ተለክቶ የተሰጠንን ጊዜ በአግባቡ ለመጠቀም ከሚረዳን ዋና ዋና ነገሮች ውስጥ አንዱ ጊዜው ለእኛ የተሰጠበትን ዓላማ ማወቅ ነው ብለን ከላይ ተመለከትን። ሌላኛው ጊዜን በአግባቡ ለመጠቀም የሚረዳን ደግሞ በእግዚአብሔር መንፈስ መመራታችን ነው። መቼም አንድ ሰው የሆነ ነገር አድርጉልኝ ብሎ ቢጠይቀን፥ የዚያን ሰው የልብ መሻት በትክክል ለመፈጸም የዚያን ሰው ትክክለኛ ፍላጎት እንዲሁም ትክክለኛ ምሪት መፈለጋችን አይቀርም። እግዚአብሔር በማንነቱ መሪ አምላክ ነው። ይሄንን ማንነቱን የእስራኤልን ሕዝብ በመራበት በ40 የምድረበዳ አመታቶች ውስጥ በስፋት ተመልክተናል። እስራኤልን ወዳሰበላቸው ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመምራት ቀን በደመና፥ ሌሊት ደግሞ በእሳት አምድ መርቷቸዋል። ምሪቱ የአቅጣጫ ምሪት ብቻ ሳይሆን፥ መንገድ ላይ በገጠማቸው ችግሮች ሁሉ ውስጥ ምን ማድረግ እንዳለባቸው በመናገር በሁሉም አቅጣጫዎች ነበር። የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔር ወዳየላቸው ወደ ተስፋይቱ ምድር የገቡት፥ በፈለጉት መንገድ ሄደው አይደለም እግዚአብሔር ሂዱ ባላቸው መንገድ ሄደው ነው። አብርሃምን፣ ሙሴን፣ ኤልያስን፣ ጳውሎስን እያንዳንዳቸውን የእግዚአብሔር ሰዎች ህይወት አስተውላችሁ ስትመለከቱ፥ የእግዚአብሔርን ሀሳብ በተሰጣቸው ጊዜ ውስጥ ፈጽመው ማለፍ የቻሉት፥ የእግዚአብሔርን ምሪት እየተከተሉ በመሄድ ነበር። ዛሬም እኛ እግዚአብሔር በእያንዳንዳችን ውስጥ ያለውን ሀሳብ ለማከናወን ግዴታ የእግዚአብሔር ምሪት ያስፈልገናል። በቃሉ ውስጥ ባሉት ህጎች እንመራለን። በተለያዩ ዝርዝር የህይወታችን ጉዳዮች ውስጥ ደግሞ የሚመራንን የእግዚአብሔርን መንፈስ እንከተላለን። ስለዚህ በዚህች ምድር ስንኖር ተለክቶ የተሰጠንን ጊዜ በአግባቡ ተጠቀምንበት የሚባለው፥ ልክ ዳዊት በተሰጠው ዘመን እና ጊዜ የእግዚአብሔርን ሀሳብ አገልግሎ እንዳንቀላፋ እኛም እንዲሁ የመጣንበትን አላማ አገልግለን ማለፍ ስንችል ብቻ ነው። ስለዚህ በተሰጠን ውስን ጊዜ ማድረግ ያለብንን እናውቅ ዘንድ ወደ ምድር የመጣንበትን ዋና አላማ ጠንቅቀን ማወቅ አለብን። ይሄንን አላማ ከግብ ለማድረስ ደግሞ በእግዚአብሔር መንፈስ መመራታችን እጅግ አስፈላጊ ነው። 

መስዋእት 

መስዋእት